Friday, March 6, 2015

ማስተርስ/ዶክተሬት እንደ መለዋወጫ እቃ! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ | የካቲት 2007
ልጄ አስራ ሁለተኛ ክፍል ስለጨረሰ የደስታዬ ተካፋይ ትሆኑ ዘንድ… የሚል ግብዣ ደርሷችሁ አያውቅም? እናንተም ፋሽኮ ቪኖ ወይንም እናትና ልጅ አረቄ ይዛችሁ ድግሱን ለማድመቅ ሳትሄዱ አልቀራችሁም – የዚያን ዕለት ጎረምሶቹ የቀለጠ ፓርቲ ደግሰው እስኪነጋ ይጨፍራሉ አሉ… ይህስ ይሁን።Fake Degrees Are Just A Few Clicks Away  Read more: http://www.care2.com/causes/fake-degrees-are-just-a-few-clicks-away.html#ixzz3TWjawZMT
ድህረ ምረቃ ፕሮግራም ላይ መሆኑን አንድም ቀን ሲናገር ሰምታችሁ የማታውቁት በቅርብ የምታውቁት ሰው ፣ እንዲያውም በመደበኛ ትምህርት ከስንተኛ ክፍል ነበር? አቋርጦ ወደ ሄደበት ሄዶ (ጫካ ወይንም ምርኮ) ግን የዛሬ ‘ሹም’ ‘የማስተርስ ፣ ዶክትሬት ዲግሬዬ በፖሰታ ስለደረሰኝ የደስታዬ ተካፋይ እንድትሆን ብሎ ቢጠራችሁስ? ይኼ ሰው ድሮ ትምህርት ቤት የተመዘገበበት ስም ሌላ ነበር… አሁን ደግሞ አዲስ ስም ብቻ ሳይሆን አዲስ ማዕረግ ፣ አዲስ ቤት ፣ አዲስ መኪና… ምኑ ቅጡ… ባናቱ ላይ ዲግሪ ሸምቶበታል።
ይድረስ ለተከበሩ… አስፈላጊውን ክፍያ ስላጠናቀቁ የ ማስተርስ ዲግሪዎን አያይዘን ልከናል – ለዶክተሬት ዲግሪዎ ተመልሰው እንደሚመጡ ተስፋ እናደርጋለን – የዋጋ ቅናሽም እናደርግሎታለን – ስለ ደንበኝነታችን ሲሉ አገልግሎታችንን ለስራ ባልደረቦችዎ እንዲያስተዋውቁልን ትብብሮን እንጠይቃለን – ለዚህም ተገቢውን ወሮታ እንከፍላለን – ያስታውሱ ‘ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ’ – ሴንቸሪ ዩንቨርሲቲ
ታዲያ እርሶም ለምርቃቱ ተጋብዘዋል – በተጠራው ድግስ ላይ ‘…ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን የት ነበር የጨረስከው ፣ ማትሪክ ውጤትህስ ስንት ነበር ፣ የመጀመሪያው ዲግሪህስ… ያጠናኸው ፣ የተመራመርከው እና መቸ ያዘጋጀኸው መመሪቂያ ቴሲስ ነው ለዚህ ያበቃህ?…’ ብላችሁ ትጠይቃላችሁ ወይስ ድግሱን ተቋድሳችሁ …እንኳን ለዚህ አበቃህ ብላችሁ መርቃችሁ ትመለሳላችሁ?
አነሳስቶ ላስጀመረን ፣ አስጀምሮ ላስጨረሰን ተብሎ ባደባባይ በግልፅ ሳይተያዩ ማስትሬት እና ፒኤችዲ እንደ መለዋወጫ እቃ ‘…ኦን ላይን ኦርደር…’ ማድረግ የወቅቱ የወያኔ ሹማምንት ልዩ መታወቂያ መሆኑን ስናይ ‘ኦ ዲግሪ ሆይ ከስምሽ ጀርባ ስንት ደደብ መሸገ’ እንድንል ያስገድደናል። ባንድ ጀምበር ሚሊየነር ፣ ባንድ ጀምበር ጄነራል እናም ባንድ ጀምበር ዶክተር እገሌ መባል ወያኔአዊ ተፈጥሮ ያመጣብን በሽታ ነው። እነኝህ ሰዎች በየመስኩ በሚፈጥሩት ስፍር ቁጥር የሌለው የተዛባና ህገ ወጥ አሰራር ጉዳቱ ውሎ አድሮ አገሪቱ ላይ በሁለንተናዊ መልኩ እየተንፀባረቀ መሆኑን ለመናገር የሚያስቸግር አይመሰለኝም። አዲሱ ሚሊየነር በሙስና እና ነጠቃ ላይ የተገነባ መሆኑ ፣ ጄነራሉ ችግር ሁሉ የሚፈታው በጠመንጃ ብቻ ነው ሲል የቁጩ ማስተርስ እና ዶክተርም የነሲብ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ሲያረቅ ሲያማክር… እንዲያው ተያይዞ ገደል መግባት መሆኑ ቁልጭ ብሎ አይታያችሁም?
‘…ለኢህአዴግ ታማኝ እስከሆነ ድረስ ማይም እንኳ ሚኒስትር መሆን ይችላል…’ ያለው ማን ነበር? ሙት ወቃሽ እንዳልሆን ብዬ እንጂ ይኼ ድኩም ራዕይ የተሰነቀው ገና ከጠዋቱ እንደነበር አትዘንጉ ለማለት ነው። የአሳ ግማቱ ከወደ አናቱ!!
አንኳንስ ዶክተሬት ስምንተኛ ክፍል ሲጨርሱ ካባ ለብሶ ፎቶ መነሳት ፣ የምርቃት ቀን ደግሞ ሽክ ባለ ልብስ ፣ ባጌጠ አደራሽ ፣ ሞቅ ደመቅ ባለ ስነስርዓት ዘመኑን መቋጨት እዚህ በምእራቡ አለም ጭምር የተለመደ ነው። ከዩንቨርሲቲ ሲመረቁ ደግሞ ስርዓቱ ለየት ይላል – ይኼ ሁሉ የሚደረገው ግን አንድም ትምህርት በአግባቡ የተሰጠ ለመሆኑ ይፋዊ ማረጋገጫ ለመስጠት ሲሆን – ሽፍንፍን ፣ ድብቅብቅ ተመርቂያለሁ ማለት ባካዳሚው አለም ሆነ በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነው። ይህን ስል በወያኔ ተቋማት አደባባይ የተመረቀ ሁሉ ብቃቱ ተረጋግጧል ማለቴ አይደለም።
ወያኔ ሁሉንም ዘዴ እንደ አስፈላጊነቱ ይጠቀምበታል። ከገበያ መሸመት ያለባቸው ሹሞች በጀት ተይዞላቸዋል – በተጠረቡ ቤቶች ውለው አድረው ‘የሚመረቁ’ ደግሞ አሉ… ከሲቪል ኢንሲቲትዩት… ከዚህ ሰፈር ከዚያ ሰፈር ኮሌጅ… ከዚህ ከዚያ ህዝቦች ዩንቨርሲቲ… ኮብል ስቶን ጠራቢ ምሩቃን ከታማኝ የወያኔ ካድሬ ምሩቃን ጋር ተማክረው ስለጉዳዩ የበለጠ ሊነግሩን ይችላሉ።
በምዕራቡ የትምህርት አለም ግን ልጆቻችሁን አስተምረን እዚህ አድርሰናል ፣ አዘጋጅተናል ፤ ኑ ተረከቡን የሚል ጥሪ ለወላጆች ሲቀርብ – ወጣቶቹ ለመጪው የከፍተኛ ትምህርት ዘመን ወይንም ለላቀ ሀላፊነት መዘጋጀታቸውን ለማብሰር ብቻ ሳይሆን ጠንክረው በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁትን በአርአያነት በአደባባይ በመሸለም ሌሎችም እንዲተጉ ለማበረታታት ጭምር ነው። ይህም የሚደረገው አለምክንያት አይደለም።

No comments:

Post a Comment