Thursday, May 28, 2015

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን ሲወዳደሩ ከነበሩት እጩዎች መካከል የኢትዮጵያው የገንዘብ ሚኒስትር ሶፊያን አሕመድ ተሰናበቱ።

ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-እንደ አዲስ ስታንዳርድ ዘገባ እየተካሄደ ባለው ዓመታዊው የባንኩ የቦርድ ስብሰባ ላይ ነው ለፕሬዚዳንትነቱ ሲወዳደሩ ከነበሩት ስምንት ዕጩዎች መካከል የገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፊያን አህመድ የሴራውሊዮኗን ሳሞራ ሚሸል ካማራን ተከትለው ሁለተኛው ተሰናባች ሆነዋል።
ቦርዱ እንደ አውሮፓያኑ አቆጣጠር ባለፈው ፌብሩዋሪ 11 ቀን አቢጃን በሚገኘው የባንኩ ዋና ጽህፈት ቤት ባደረገው ስብሰባ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትርን ጨምሮ ስምንት ስዎች በእጩነት መቅረባቸው ይታወቃል።
ይህም የሆነው አቶ ሶፊያንና ሌሎቹ ዕጩዎች ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሩዋንዳ-ኪጋሊ በተካሄደው የባንኩ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ለመሆን እንደሚፈልጉ ፍንጪ በማሳየታቸው ነበር።
ላለፉት አስር አመታት ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ዶናልድ ካቤሩካ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።
ጋዜጣው እንደዘገበው የተለያዩ አገር መንግስታት በእጩነት የቀረቡት ዜጎቻቸው እንዲመረጡ ቅስቀሳ ቢያደርጉም ፣ የኢህአዴግ መንግስት ግን ለአቶ ሶፍያን ቅስቀሳ አላደረገም። መንግስት ለአቶ ሶፍያን ቅስቀሳ ለማድረግ ለምን እንዳልፈለገ የገለጸው
ነገር የለም። አቶ ሶፍያን ለአፍሪካ ህብረት መወደዳራቸው በመጪው ጊዜ በስልጣን ላይ እንደማይቆዩ አመላካች ሆኗል

በምርጫ ቦርድ ውጤት የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሁለት ተከፍለዋል

ግንቦት ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ የግንቦት15ቱን ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉ ከተገለጸ በሁዋላ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ከሁለት ተከፍለዋል። ምንጮች እንደገለጹት በርካታ ፊደል ቀመስ አባሎቹ ኢህአዴግ አሸነፍኩ
ያለበትን የድምጽ ልዩነት አልተቀበሉትም። ውጤቱን የሚቃወሙ የግንባሩ አባላት ” ህዝቡ ከእንግዲህ በሰላም መንግስት እቀይራለሁ የሚለው እምነቱ ተሟጦ የሃይል አማራጭን ብቻ እንዲመለከት ከማድረጉም በላይ፣ የሃይል አማራጭን
የሚከተሉ ሃይሎች በህዝቡም ሆነ በአለማቀፉ ማህበረሰብም የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል” በማለት ለድርጅቱ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ተገኘ የተባለውን ውጤት ከመደገፍ አልፈው፣ ህዝቡ እንዴት ለተቃዋሚዎች ይህን ያክል ድምጽ ሊሰጥ ቻለ በማለት በቁጭት አስተያየት የሚሰጡ ደጋፊዎች መኖራቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
ኢህአዴግ እያሰባሰበ ባለው መረጃ ላይ እንደተገለጸው፣ አንዳንዶች ” ይህ ህዝብ ምን አይነት ልቡ የማይታወቅ ከሃዲ ህዝብ ነው! እንዴት ይሄን ሁሉ ልማት እያዬ ለተቃዋሚ ድምጹን ሊሰጥ ቻለ?” የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ቦርድ ራሱ ባወጣው ሰሌዳ መሰረት የምርጫውን ውጤት መግለጽ የነበረበት ግንቦት21 ቢሆንም፣ የግንቦት20 በአልን ለማድመቅ እንዲረዳ በሚል ከእቅዱ በፊት እንዲገለጽ መደረጉን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ
ዘጋቢያችን ገልጿል።
ኢህአዴግ በየክልሉ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የፌሽታ በዓላትን አዘጋጅቷል። ትናንት የገዢው ፓርቲ ደጋፊ አርቲስቶች ያዘጋጁት የኪነጥበብ ምሽት በብሔራዉ ቲያትር ተካሂዷል፡፡፡ በርካታ የፌዴራል የመንግስት መ/ቤቶች በተለያዩ ሆቴሎች
በዓሉን ለማክበር ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምርጫ ቦርድ የኢህአዴግን አሸናፊነት ቢያውጅም መድረክ የተባለው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብስብ የምርጫውን ውጤት አልተቀበለውም። ድርጅቱ ምርጫው አነስተኛ የሚባሉ መስፈርቶችን እንኳ ያላሟላ በማለት አጣጥሎታል። መድረክ
በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ገለልተኛ የሚባሉ ሰዎች ተመርጠው መምርራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።
ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫውን በተመለከተ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ያለው ነገር የለም። መንግስት የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎችን እያዋከበ በማሰር ላይ መሆኑ፣ ፓርቲውን አጣብቂኝ ውስጥ ሳይከተው አልቀረም። ሰማያዊ የምርጫውን
ውጤት ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም።
የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን በተመለከተ በርካታ እጸጾችን አውጥተው ቢገልጹም፣ ከኢህአዴግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደማያቋርጡ አስታውቀዋል። የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጣው መግለጫ ዲፕሎማቶች
በምርጫ ታዛቢነት እንዳይሰታፉ መከልከላቸው፣ ምርጫው አሳታፊ አለመሆኑንና የተለያዩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መታሰራቸውን በመግለጫቸው አመልክተዋል።
በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ በርካታ አስገራሚ ክስተቶች ለኢሳት እየደረሱ ነው። ግንቦት12 ቀን 2007 ዓም በአዲስ አበባ ልዩ ቦታው ላንቻ ወይም ጠመንጃ ያዥ ነዋሪ የሆነ አንድ የ12 ዓመት ህፃን የኢህአዴግን የምርጫ መልዕክት ያየዘ
ፖስተር ከተለጠፈበት ግድግዳ ላይ ቀደሃል በሚል 6 ወር ተፈርዶበታል።
በአዲስ አበባ ችሎት በሚባል ቦታ አርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ሁለት ማየት የተሳናቸው ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ወጣቶቹ የተያዙት አንደኛው ሙሉ ሰማያዊ ልብስ ለብሶ በመውጣቱ በተፈጠረው አተካራ ነው። የአካባቢው
ሴት ካድሬ አንደኛውን ማየት የተሳነው ወጣት “ለምን ሰማያዊ ልብስ ለበስክ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነሆይ?” በማለት ጥያቄ ስታቀርበለት፣ ጓደኛው “ምን አገባሽ ምንስ ብለብስ!” የሚል መልስ መስጠቱን ተከትሎ፣ ግለሰቧ በብስጪት
ለደህንነቶች ባስተላለፈችው ጥቆማ መሰረት ሁለቱም ወጣቶች በድንገት ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ ታስረው ይገኛሉ።
መነን መሰናዶና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም ፀሃይ ጮራ ት/ቤት ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው 20 መምህራንና 30 ተማሪዎች የሰማያዊና የአንድነት ፓርቲ አባላት ናቸው በሚል ዝርዝራቸው ለጸጥታ አካላት ተልዕኮ በልዩ ሁኔታ ክትትል እንዲደረግባቸው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከምርጫ በፊት ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበርም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

Thursday, May 14, 2015

በቴፒ 5 ሰዎች ተገደሉ

በጋምቤላና ደቡብ ክልል ድንበር አካባቢ የሪ በምትባል ቀበሌ 7 ሰዎች በተገደሉ ማግስት ሌሎች 5 ሰዎች ደግሞ በቴፒ ከተማ እንድሪስ ቀበሌ ውስጥ ከሌሊቱ 8 ሰአት ላይ በጥይት ተደብድበው መሞታቸውን የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት ከሟቾቹ መካከል አባትና ልጅ ይገኙበታል። ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ ገዳዮቹ ፖሊሶች ናቸው። ነዋሪዎች እንደሚሉት ሰዎቹ ይተገደሉት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አማጽያንን ያስጠጋሉ፣ ይደግፋሉ ተብለው ነው። ኢሳት ለከተማው ፖሊስ በመደወል ለማጣራት ሙከራ ቢያደርግም አልተሳካም።
ኢሳት ከሶስት ቀናት በፊት “ከመስከረም ወር ጀምሮ በቴፒና አካባቢዋ ያለው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውንም፣ በእየለቱ በከተማዋ ውስጥ የጥይት ድምጽ እንደሚሰማና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሸኮ መዠንገር ነዋሪዎች እየፈለሱ ወደ ቴፒ ከተማ በመግባት ላይ መሆናቸውን ” ዘግቦ ነበር።
ነዋሪዎች ጸጥታውን የሚያስከብርልን ሃይል አጥተናል በማለት በተደጋጋሚ አቤቱታ ያሰማሉ።

Monday, May 4, 2015

የኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎች በድርጅታቸው ግራ ተጋብተዋል

ሚያዝያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር የወጣው ህዝብ ተቃውሞውን ወደ ኢህአዴግ መንግስት ካዞረ በሁዋላ፣ ገዢው ፓርቲ ተቃውሞውን ያስነሳው በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ
የሚታገለው ሰማያዊ ፓርቲ ነው በማለት የከፈተው ሰፊና አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ የህዝቡን አመለካከት ሊቀይር አለመቻሉ ከፍተኛ ካድሬዎችን ስጋት ላይ ጥሎአቸዋል፡፡
በመስቀል አደባባይ የታየውን ህዝባዊ ቁጣ  ሰማያዊ ፓርቲ የቀሰቀሰው የመንደር ሁከት ለማስመሰል በስሩ በሚገኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ፕሮፖጋንዳ የሰራ ቢሆንም ፣ ፕሮፓጋንዳው ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የራሱን አባሎች ማሳመን አለመቻሉ ከፍተኛ
ካድሬዎችን ድንጋጤ ላይ ጥሎአቸዋል።
በአዲስአበባ አስተዳደር በተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች  ይህንኑ የሕዝብ ተቃውሞ በማስመልከት ሰማያዊ ፓርቲ ያቀነባበረው መሆኑን በመግለጽ ሁኔታውን ለማውገዝ ታስቦ ሰሞኑን ተከታታይ ስብሰባዎች የተካሄዱ ቢሆንም አጥጋቢ ውጤት ሊገኝባቸው አልቻለም፡፡
በተለይ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ጭምር ፍረጃው አሳማኝ አለመሆኑን በመጥቀስ ሕዝቡ በተለይ በመልካም አስተዳደርና በኑሮ ውድነት ችግሮች ውስጥ ሆኖ መቃወሙ የሚጠበቅ እንደነበር፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ይልቅ ወደውስጣችን በመመልከት ችግሩን ካልቀረፍን
ከዚህም የባሰ ችግር ሊገጥመን ይችላል በሚል የተንጸባረቁ ደፈር ያሉ አስተያየቶች ያልተጠበቁ በመሆናቸው የመድረክ መሪ ካድሬዎችን ጭምር አስደንግጦአል፡፡