Wednesday, January 21, 2015



ኢትዮጵያን   እየመሩ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙሉ በጥቂት ቀናት ትምህርት ብቻ  ከአንድ የውጪ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ እንዲያገኙ መደረጋቸው ተመለከተ።

ጥር ፲፫(አስራ ሦስት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሀገሪቱ የምትመራበትን  ፖሊሲ ከመጠምዘዝ ጀምሮ ድርጊቱ በሀገርና በህዝብ ላይ የከፋ ተጽእኖ እንዳለው የተገነዘቡ ኢትዮጰያውያን በዩኒቨርሲቲው ላይ  የተቃውሞ ዘመቻ እያስተባበሩ ነው።
አዲስ አበባ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ሊደር ሺፕ ኢንስቲትዩት አማካይነት የሚቀርቡለትን ባለስልጣናት በአጭር ቀናት ኮርስ በማስተርስ ዲግሪ እያንሸበሸ ያለው ፤በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘው የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ነው። በአይ ኤል አይ ድረገጽ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሁሉም የሀገሪቱ ባለስልጣናት በቀናት ኮርስ  ከአንድ ትምህርት ቤት ማለትም ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ  የማስተርስ ዲግሪ እንዲወስዱ ተደርገዋል።
እነሱም፦አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሱ ለገሰ፣የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትርና የ አሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ በረከት ስምኦን፣የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር፣የቀድሞው የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ፣ የቀድሞው የ አዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣የ ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሸፈራው ተክለማርያም፤ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን፣ የትምርት ሚኒስትር ሽፈራው ሽጉጤ፣ የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ሚኒስትር አስቴር ማሞ፣ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትርና የ አሁኑ የ አዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣የሴቶች፣ የህጻናትና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዘነቡ ታደሰ፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባ ኤ ካሳ ተክለብርሀን፣የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደሴ ዳልክዬ ዱካሞ፣የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አብርሐም ተከስተመስቀል፣የቀድሞ መከላከያ ሚኒስተርር ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ዳውድ መሀመድ አሊ፣የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ተከስተ ረባ አያና፣በፌዴሬሽን ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙፈሪያት ካሚል አህመድ እና በመከላከያ ሚኒስትር የምእራብ እዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል  ብርሀኑ ጁላ ጋላቻ ናቸው።
በኢንተርናሽናል ሊደር ሽፕ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ ከተዘረዘሩት ከነኚህ ባለስልጣናት ባሻገር  የሀገሪቱ ጀነራሎችና የጦር አዛዦች እንዲሆም የየዞኑ የቢሮ ሀላፊዎች በሙሉ  በሶስትና አራት ቀናት ኮርስ ከዚሁ ከግሪንዎች ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ መያዛቸውን   በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲው መምህር የነበሩት ዶክተር ታደሰ ብሩ  ይናገራሉ።
የማስተርስ ዲግሪ ከወሰዱት ከነኚህ ሹመኞች መካከል  በጣት የሚቆጠሩ ጥቂቶች በራሳቸው የተማሩ ቢሆንም፤ በርካታዎቹ የ2ለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚገባ ስለማጠናቀቃቸው ትክክለኛ ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም። ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከትምህርት ሚኒስትሩ ጀምሮ አሉ ለሚባሉ የሐገሪቱ ሹማምንት ሁሉ የማስተርስ ዲግሪ በዚህ መልክ መታደሉ በሀገሪቱ ፖሊሲዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ያለው ተጽ እኖ ከፍተኛ እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ያብራራሉ።
የግሪንዊች ዩኒቨርሲቲንም  “ሀገሪቱን እጅ የጠመዘዘ፣ሀገሪቱን እኪሱ ያስገባ ተቋም”ብለውታል ዶክተር ታደሰ። የትምህርት ሚኒስትሩ ዕፈራው ሽጉጤ ከዚሁ ከግሪንዊች ተቋም መመረቃቸው የሚፈጥረን የጥቅም ግጭት  ዶክተር ታደሰ ሲያብራሩም፦ ይህ ድርጊት ለዩኒቨርሲቲውም እፍረት ነው፤ለሀገራችንም ጉዳት ነው ያሉት ዶክተር ታደሰ፤ የዩኒቨርሲቲውን ድርጊት ለመቃወም  ፒቲሺን  ፈርሞ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን በማውሳት፤ ኢትዮጰያውያን  በተቃውሞ ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ የጥምቀት ባህል ላይ የቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖት የታቦት ሽኝት ላይ ከወያኔ ደጋፊዎችና ሰላዮች ጋር በተፈጠረ ግጭት በርካታ ወገኖች የቆሰሉ ሲሆን የአንድ ሰው ህይወት አልፏል። በግጭቱ ወቅት የፌዴራል ፖሊሶች ከወያኔ ደጋፊዎች ጎን ተሰልፈው ወጣቶችን በፋሽስታዊ ጭካኔ ግንባራቻው እስኪተረተር ሲደበድቧቸውና በመኪና ሲገጯቸው ይታይ ነበር። በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የወያኔ ፖሊሶችን ወከባ በመቋቋም ሰማያዊ ቲሸርታቸውን ለብሰው በዓሉን ለማክበር ወጥተዋል።

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ነፃነትን የማስመለስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
• ዜጎች የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ ጥሪ አቅርቧል
• ‹‹ምህዳሩ ካልተስተካከለ ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረውም ቢሆን ከምርጫ ልንወጣ እንችላለን››
የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹በነፃነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› ዘመቻው ነፃነትን የማስመለስ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ፡፡ ትብብሩ ዛሬ ጥር 12/2007 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ አፈና እና ጫና እያደረጉ ቢሆኑም ነፃነትን ለማስመለስ የያዘውን ግብ ለማሳካት ወደኋላ እንደማይል ገልፀዋል፡፡ ‹‹የኢህአዴግ ጨካኝነትና የምርጫ ቦርድ አጋፋሪነት ሊቀጥል ይችላል›› ያሉት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ሆኖም የትግሉ አላማ ኢህአዴግን ማጋለጥ በመሆኑ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት እየከፈሉ ትግሉን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ‹‹ህዝቡ ካርድ እንዲያወጣ ጥሪ ስናደርግ የፖለቲካ ምህዳሩ ተስተካክሏል እያልን አይደለም፡፡ እኛ አሁንም እያነሳን ያለነው የትግል ጥያቄ ነው›› ያሉት የትብብሩ ም/ል ሊቀመንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ የትብብሩ የትግል አላማ ይህን የተዘጋ ምህዳር ማስከፈት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ትብብሩ ‹‹የትግሉ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት የሆንከው መራጩ ህዝብ ነጻነትና ክብርህን ለማስመለስ በምናደርገው ትግል በንቃት እንድታሳተፍ፣ ዛሬውኑ በመመዝገብ የሥልጣን ባለቤትነትህን የምታረጋግጥበትንና ይህን አምባገነናዊ ሥርዓት የምትቀጣበትን ትጥቅ ‹‹የምርጫ ካርድህ››ን በእጅህ እንድታስገባ›› ሲል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እንዲሻሻሉ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች የማይመለሱ ከሆነ እና ምህዳሩ ካልተስተካከለ ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረውም ቢሆን ከምርጫ ልንወጣ እንችላለን ብሏል፡፡
ምህዳሩ ተዘግቷል እያላችሁ ህዝቡ ምርጫ ካርድ እንዲያወጣ መጠየቅ አይጋጭም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ‹‹ዜጎች ምርጫ ካርዱን ማውጣታቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይጠቅማል፡፡ ኢህአዴግ አንድ ለአምስት እየጠረነፈ የምርጫ ካርድ በማስወጣቱ ህዝቡ ተስፋ ሊቆርጥ አይገባም፡፡ ትግሉ ሲጠናከርና ሂደቱ ሲቀርብም ኢህአዴግ እጠቀምበታለሁ ያለውን ሁሉ የማንጠቀምበት ምክንያት የለም፡፡ ለመምረጥም ሆነ ላለመምረጥ ምርጫ ካርድ ማውጣቱ አስፈላጊ ነው፡፡ የመጨረሻ ውሳኔው በሂደቱ የሚወሰን ይሆናል፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ግርማ በቀለ በበኩላቸው እስካሁን ትብብሩ ያደረገው ትግል ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ጎን የቆመበት መሆኑን ያረጋገጡበት እንደሆነ ገልጸው ሂደቱን ለመወሰን ህዝቡ ምርጫ ካርዱን አውጥቶ መጠባበቅ እንዳለበትና ምርጫ የመግባትና አለመግባት ጉዳይ ለመወሰን ጊዜው ገና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ከመግባትና ካለመግባት ባሻገር ትግሉን በማጠናከር ኢህአዴግ አንድም በግልጽ በመሳሪያ ብቻ እገዛለው እስኪል አሊያም በምርጫና በመሳሪያ መካከል ያለውን አታላይ መንገድ ትቶ ዴሞክራሲያዊ መንገድን እንዲመርጥ ማድረግ ትልቅ ድል ነው፣ ያሉት የትብብሩ ሊቀመንበር የትግሉ ዋና አላማ የኢህአዴግን አታላይነት ማጋለጥ ነው ብለዋል፡፡